አጋርፋ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በ2014/2015 የምርት ዘመን ከ1200 ሄክታር በላይ መሬት በሰብል በመሸፈን በአሁኑ ሰዓት ምርት በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት በማሽነሪ እጥረት በምርት ሳይሸፈን የነበረው መሬት በአሁኑ ጊዜ የእርሻ ማሽነሪዎችን በውስጥ ገቢ በተወሰነ ደረጃ በማሟላት የሚለማውን መሬት በሄክታር ከፍ በማድረግ ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለፋብሪካ ግባቶች እና ለዘር ብዜት ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡

በዚሁም መሠረት ፡-

  • ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በመቀናጀት ኢቦን የሚባል የቢራ ገብስ መስራች እና ቅድመ መስራች የቢራ ገብስ የማባዛት ሥራ፣
  •  ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር በመቀናጀት የብቅል ገብስ ዝርያ HB1963 የማምረት ሥራ፣
  • ከቦርት ማልት ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር በመቀናጀት ትራቭለር እና ሄኔሪኬን የተሰኘ ዝርያ ገብስ የማባዛት ሥራ፣
  • ከሶፍሌት ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግል ማህበር ጋር በመቀናጀት ፕላኔት የሚባል የቢራ ገብስ የማልማት ሥራ ተከናውኖ በአሁኑ ጊዜ ምርቱን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡

ከኮሌጁ ጋር በቅንጅት በውል ስምምነት እየሠሩ ካሉት ከላይ ከተጠቀሱት ድርጅት ፣ከባሌ ዞንና ከአጋርፋ ወረዳ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች፣በአከባቢው ካሉ የአጎራባች የቀበሌ ገበሬ ማህበራት የቀበሌ አመራሮች በተገኙበት በግብርና የምርት ማምረት ሥራ የላቀ አፈፃፀም ያላቸው ገበሬዎችና በኮሌጁ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቢራ ገብስ የለማውን ሰብል፣የማረቆ በርበሬ እና በተለያዩ የሰብል፣አትክልትና የእንስሳት መኖ ምርምር የሰርቶ ማሳያ ጣቢያን በመጎብኘት እየተሰራ ያለውን የማልማት ሥራ ህዳር 03 ቀን 2015 ዓ.ም በመስክ ጉብኝት ተመልክተዋል፡፡

ኮሌጁ በሀገሪቱ የሚታየውን የቢራ ገብስ እጥረት ለመሙላት ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ጋር ቅንጅት ፈጥሮ ከ1200 ሄካታር በላይ የሆነ መሬት የቢራ ገብስን እያለማ መሆኑንና የአከባቢው አርሶ አደሮችም የቢራ ገብስ ምርጥ ዘርን በቀላሉ አግኝተው እንዲያመርቱ ሙያዊ ድጋፍን ጨምሮ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ስራዎች እየሰራ እንደሆነና በቀጣይም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንሠራለን ሲሉ በጉብኝቱ ላይ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ጫላ ፈዬራ ገልፀዋል፡፡

ለተማሪዎች የመስክ ሙከራ ትምህርት ይሆን ዘንድ እና የውስጥ ገቢን ለማሳደግ በሚሰሯቸው ሥራዎች ላይ በርካታ ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው፣የአከባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ የአትክልት ምርጥ ዘሮችን በቀላል ዋጋ ገዝተው እንዲያለሙ የሙያ ምክር ስልጠናና ድጋፍ በማድረግ በርካታ የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በመስራት ላይ እንዳለ የቴክኖሎጂ ብዜትና ሽግግር ም/ዲ አቶ ፍራኦል ኤደኦም በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡

በኮሌጁ አቅራቢያ ያሉ አርሶ አደሮችም በመስክ ምልከታው ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የሙያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው እንዲሁም የተለያዩ የምርጥ ዘር በተመጣጣኝ ዋጋ በማግኘት የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልፀው ተቋሙ ለአከባቢው ያለው ጠቀሜታ ትልቅ በመሆኑ ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል፡፡

Leave a Comment